ከቅርብ ግዜ ወዲህ ከነጮቹ ከኮረጅናቸው ትውፊቶች
አንዱ ቫላንታይን ነው፡፡ ቫላንታይንን ተከትሎ ሆቴሎቻችን ሽቀላ ተመችቶአቸዋል፡፡ ምግብና መጠጥን ጨምሮ ልዩ የቫላንታይን ቀን ዝግጅት
በሶስት መቶ ብር ብቻ የተለመደ ማስታወቂያ ነው፡፡ ይቅርታ ይህቺ እኛ ሰፈር ያለችዋ ዋጋ ናት፡፡
እዛኛው ሰፈሮች ከሁዋላዋ አንድ ዜሮ በመጨመር
ተባበሩኝ፡፡
ታድያ የቫላንታይን አካባቢ የቀይ ልብስ ሲያንስ
ሲያንስ በጥፍ ሲበዛ ከዚያም በላይ ይጨምራል፡፡ ሌላ ጊዜ ጥግ ላይ ተጥላ የነበረች ቀይ ልብስ ክብር ታገኛለች የዛ ሰሞን፡፡ ብዙዎቹ
ካፌዎች እና ባሮች በቀይ ቀለም ያሸበርቃሉ ፡፡ ቀይ አበባ በሌሎቹ አበቦች ላይ ትነግሳለች፡፡
ይሁንና ቫላንታይን በኪነጥበብ ሰዎች ዘንድ በየአመቱ
ማጨቃጨቁዋ አልቀረም፡፡ አምርረው የሚከራከሩ ተቁአሚዎች ቫላንታይን የባህል ወረርሽኝ ነው፡፡ በፍቅር ሰበብ የተሰነዘረ የባህል ማጥፊያ
ነው ሲሉ ይደመጣል፡፡ ቫላንታይንን ሰበብ በማድረግ በየመንገዱ መሳሳም ምን ይሉታል ብለው ይሞግታሉ፡፡
ሌሎች ምነው ፍቅር ቢወሳ ፍቅር ቢዘከር ስለፍቅር
መስዋእትነትን እንደ ቄስ ቫላንታይን ያሉ ቢታወሱ ምን ችግር አለ ፡፡ ይህ አላስፈላጊ ወግ አጥባቂነት ነው ብለው ሲሞግቱ ይደመጣሉ፡፡
ምነው የጥምቀት ቀን ቆነጃጂት እምር ብለው ለመታየት ኮበሌውንም ለመማረክ ፡ ግፋም ሲል ከከንፈር ወዳጆቻቸው ጋርስ ሲጫወቱ ይፈቀድምላቸዋል
አይደል ብለው ይሞግታሉ፡፡
ለነገሩ የሱሬውን ባትሌት ዝቅ ሳይሆን ልቅቅ አድርጎት
ትርጉሙን ለማያውቀው ፡በደረቱ ላይ የ ሰማይ ስባሪ የሚያክል ሰንሰለት አጥልቆ ለምን እንዳደረገው የማያስረዳ ፡ ኮረዳዋን ይመስል
ሎቲ አጥልቆ ጸጉሩን አንጨፍሮ ለምን ሲባል እኔንጃ የሚል በበዛበት በዚህ ዘመን ቫላንታይንን በጥርጣሬ ሰዎች ለምን አዩት አይባልም፡፡
ነገር ግን ሁሉም ነገር ልክ አለው ፡፡ ጥርጣሬም
ልክ አለው፡፡ ለባህል መቆርቆርም ልክ አለው፡፡ ፍቅር የሁሉ ነገር ገዢነው ካልን ፡ፍቅር ከሁሉ ይበልጣል ካልን ፍቅርን የምንዘክርበት
አንድ ቀን ቢኖረን ምን ይለዋል ? ምንም!! ቸር እንሰንብት፡፡
No comments:
Post a Comment